ከንጽህና ጉድለት ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮችን ለመከላከል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚገባ ተመላከተ

መጋቢት 8/2018(አረቅጥ)በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ የጽዱ ኢትዮጵያ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሔዷል

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ እንደገለጹት በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ላይ የአካባቢ ንጽህና ወሳኝ ነው ብለዋል።

የአካባቢ ንጽህና ሲጠበቅ በሽታ የመከላከል አቅም ይጨምራል ያሉት ምክትል ኃላፊው በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው መረጃ እንደሚያመላክተው ከንጽህና ጉድለት ጋር ተያያዥነት ባላቸው የጤና ችግሮች ምክንያት በየአመቱ ከ 435ሺ በላይ ህጻናት ይሞታሉ በማለት ጠቅሰዋል።

በአፍሪካም ከዚሁ ጋር በተያያዙ የጤና ጠንቆች ምክንያት ለህክምና የሚወጣው ወጪ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ኪሳራ እያስከተለ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

በሀገራችን ከ22 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች መጸዳጃ ቤት አይጠቀሙም ያሉት አቶ አሸናፊ ይህም በጤናው ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይ ከ5 ዓመት በታች የሚሆኑ ህጻናት ከንጽህና ጉድለት ጋር በተያያዘ ለሞት ይዳረጋሉ ሲሉም አብራርተዋል።

ተጋላጭነትን በማያስከትል መልኩ የመጸዳጃ ቤቶች ግንባታ ማካሔድ ወሳኝ ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው ይህም በህብረተሰቡ ጤና ላይ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚኖረውም አመላክተዋል።

ህብረተሰቡ ሜዳ ላይ የመጸዳዳትን ችግር እንዲገነዘብ መስራት ይገባል ያሉት አቶ አሸናፊ ለህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደግሞ ሞዴል ሊሆኑ እንደሚገባም አስረድተዋል።

የጽዱ ኢትዮጵያን ግብ ለማሳካት የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጎልበት ተገቢ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *