ጉመር ,ጉራጌ ዞን
ሰነን ደብረ ጸሀይ ቅድስትማርያም ቤተ-ክርስትያን አመሰራረት
ኢትዮጵያ የባለብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ሀይማኖቶች ባለቤት ናት፡፡ከእነዚህ ሀይማኖቶች መካከል የክርስትና ሀይማኖት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የክርስትና ትምህርት በስፋት እየተሰጠና እምነቱ እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋፆ አበርክተዋል፡፡
ከእነዚህ ጥንታዊ ቤተክርስትያን መካከል የሰነን ማርያም ቤተ-ክርስትያን አንዱ ነው፡፡በሰነን ማርያም ቤተክርስትያን ከጉመር ወረዳ ዋና ከተማ አረቅጥ በስተ ሰሜን በ17 ኪ/ሜ ከዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤ በ73 ኪ/ሜ በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ትገኛለች፡፡ሰነን ማርያም ቤተክርስትያን በድርቦና ሰነን ቀበሌ ልዩ መንደሩ ሰነን መንደር ላይ ትገኛለች፡፡ታሪካዊ ከሆኑ ስፍራዎች አንዱና ዋነኛው ቀዳሚ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡የሰነን ማርያም ቤተክርስትያን የተመሰረተው በ1887ዓ.ም እንደሆነ አባቶች ያስረዳሉ አመሰራረቱም አጼ ሚኒሊክ በጦርነት ግዛት ለማስፋፋት ሰራዊታቸውን ይዘው እየተንቀሳቀሱ በነበረበት ሰዓት በአካባቢ ደርሰው ግዛቶች ለማስፋፋት ባደረጉት ሙከራ በቀላሉ አልተረከቡትም፡፡በወቅቱ በጀግንነቱ የሚታወቀው ከአበጋዝ ዳርሳሞ ጦር ጋር ከፍተኛ ጦርነት ተካሂዷል፡፡ጦርነቱም በሶስት ዙር ቢካሄድም በሶስቱም ዙር አበጋዝ ዳርሳሞ ጦር አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡
ንጉሱም ዳቁና ላይ ሆነው በርቀት በአጉሊ መነጽር የጦር ውሎ ሲከታተሉ እንደነበረ ቢታወቅም በሶስት በተካሄደው ጦርነት ሰራዊት ከፍተኛ እልቂት ደርሶበታል፡፡ከዛ በመነሳት ብዙ ሰራዊት በማለቁ አረቅጥ(አለቅጥ) ብዙ የሚል የተሰጠው የመጀመርያ ስያሜ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ጦርነቱ ሶስት ጊዜ በሶስት ጦር ‹‹አበጋዞች›› እራሶች ነው የተካሄደው፡፡በመጀመርያ እራስ መሸሻ መሪነት የተደረገ ጦርነት፣በሁለተኛ በራስ ውርጆ መሪነት መየተደረገ ጦርነት እና በሶስተኛ በራስ ጎበና ጦርነት ሲሆን በሶስቱም ዙር የተካሄደው ውግያ እግር አንገት (ጎማረ) ሆኖ እንደተገለፀው በጦሩ መሪ አበጋዝ ዳርሳሞ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ሆኖም ጦርነቱ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት አፄ ምንሊክ ከዳቁና ከፍ ካለ ቦታ ሆነው በመነጽራቸው የጦር እንቅስቃሴ እየተከታተሉ በነበሩበት ጊዜ ከፊት ሆኖ በጦሬ ላይ እልቂት እያደረሰ ያለው ማን ነው? ብለው ሲጠይቁ የጦሩ መሪ መሆኑን ተነገራቸው፡፡በእርግጥ አበጋዝ ዳርሳሞ ልዩ መልዕክት ጭምር በክንዳቸው ነበራቸው፡፡ከዛ አንጻር በምልክታቸው ነበር ንጉሱ ያወቋቸው፡፡በመጨረሻም ጦርነቱ በዚህ ሁኔታ እያለ ንጉሱም ከአማካሪያቸው ከግርማሜ ጋር መመካከር አንድ ጎማረ ይህንን ያህል እልቂት በጦሬ ላይ ካደረሰ ሙሉ ጉራጌ ቢነሳብን ማምለጫም የለንም በማለት የቀረ ጦራቸው በማሰባሰብ በማታ ጉዞ በማድረግ ወደ ከተማቸው አንኮበር ገቡ፡፡
ከዛ አንኮበር በቤተ መንግስታቸው ስለ ጦርነቱ ከመኳንንቱ እየተጫወቱ በነበረበት ወቅት በእርግጥ ለአሁን አሸንፋኛለች ወደፊት ግን አሸንፋታለሁ፡፡ነገር ግን እኔ ጀግና እወዳለሁ ጀግና ማጥፋት አልፈልግም እሷን ወዳጅ ማድረግ እፈልጋለሁ በማን በኩል ወዳጅ እናደርጋታለን? ሲሉ በሙሁር አበጋዝ ሽበታ በኩል ንጉሱ ከዳርሳሞ እንዲተዋወቁ ስለተገለጸ አበጋዝ ሽበታ አበጋዝ ዳርሳሞን ይዞ አንኮበር እንዲያመጡት ቀጠሮ ተያዘ፡፡በተያዘ ቀጠሮ መሰረት አበጋዝ ሸበታ ወደ ዳርሳሞ ጋር ሄዶ ጉዳዩ ሲያስረዳቸው ለመሄድ ቢስማሙም ህዝቡ ግን የሚበቀላቸው ስለመሰለው አትሄዱም ከፈለጉ መጥቶ እዚሁ ሁላችንም ይጨርሱን ሲሉ ዳርሳሞ አይሆንም ከንጉሱ ቃል ገብቶ ነው የመጣው በሽበቶ ችግር እንዲደርስበት አልፈልግም ከፈለገ እዛው ይግደለኝ በማለት ሌሎች ሁለት ሰዎች ተጨምረው አበጋዝ ጢቻ፣አበጋዝ ዛንጊወ ከሸበቶና ከዳርሳሞ ጋር አራት ሆነው አንኮበር ደረሱ፡፡ከዛ በኋላ አንድ ጊዜአልቀረቡም በመጀመርያ አጋዝ ዛንጊወ ወደ ንጉሱ ቢያቀርቧቸው አንቺ አይደለሽም አላቸው፡፡
በሁለተኛው አበጋዝ ጢቻን ቀረቡ አሁንም አንቺ አይደለሽም አሉ በመጨረሻ በሶስተኛ አበጋዝ ዳርሳሞ ሲቀርብ በምልክቱ አወኩት አዎ አንቺ ነሽ! ጦሬ የጨረሽው በማለት አስተርጓሚ ለአበጋዝ ዳርሳሞ በአማርኛ ወደ ጉራጊኛ ሲናገርዋቸው እኔ እንደሱ ወንድነኝ ለምን በሴት አፍ ይጠራኛል አሉ፡፡ይህንን የጉራጊኛ ቃል ወደ አማርኛ ለምንሊክ ተነገራቸው እሳቸውም በእርግጥ አንቺ ጀግና ነሽ ስለሆንሽም ላንቺ ብቻ አንተ እላለሁ አሉ፡፡ከዚያ አጠገባቸው የነበሩ መኳንንቶች የኢትዮጵያ ወንድ ሁሉ አንቺ እያላችሁ ለአንድ ጉራጌ እንዴት አንተ ትላላችሁ ብለው ሀሳብ ሲያቀርቡ ጉዳዩ ለዳርሳሞ ተነገራቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ወንዶች አንቺ የሚል ከሆነማ በማለት ወደ ተጠሩበት ጉዳይ ለምን እንደጠሯቸው ለንጉሱ ጠየቁ ንጉሱም እኔ አንቺን የጠራሁሽ ባየሁትጀግንነትሽ ልንተዋወቅ ነው፡፡ እኔ ጀግና እወዳለው ጀግና አላጠፋም ስለዚህ ልጅ አድርጌሽ ክርስትና ላስነሳሽ ነው ሲሏቸው ዳርሳሞም በጉዳዩ ተስማምተው አድረው በማግስቱ ከቅዳሴ በኋላ ንጉሱ ሰው ልከው ክርስትና እንዲነሱ ዳርሳሞ ሲጠየቁ እምቢ አሉ ፡፡ምክንያቱም እራሱ ሊያነሳኝ ነው የጠራኝ ጉራጌ ምን ይለኛል በአሽክር ክርስትና ብነሳ በማለት እምቢታቸው ገለጹ ይህን ጉዳይ ወሬው ንጉሱ ጋር ደረሰ ከዚያም ንጉሱ በመምጣት ማንሳቱ አነሳሽ ነበር ሆኖም ክርስትና ያነሳሁት እድሜ አይኖረውም አላቸው ዳርሳሞም ዛሬ አንስተውኝ ከፈለኩኝ በማግስቱ ልሙት አሉት ከዚያም በኃላ ንጉሱም ጣታቸው ይዘው ክርስትና አንስተው አባትነታቸው አረጋግጠው ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ የማርያም ታቦት ሰጥተውና ግዛቱ እንዲያስተዳደሩ ከመጌቻ -ውንቅየ በመለስ ባላባትነትን ሰጥተው ሲሸኟቸው እንግዲህ እኔ በዚህሁኔታ እየሸኘዉህ ነው፡፡
አንተስ ምን ትሸልመኛለህ ብለው ሲጠይቁ ዳርሳሞም እኔ ደሃ ነኝ ንጉሴን ለመሸለም የምችል አቅም የለኝም ሆኖም ያለኝ ይህንን ቃርቻ ከኮርቻ (ፈረስ)ልስጦት በማለት ፈረሳቸውን ሰጧቸው ፡፡ ንጉሱም በወቅቱ የዓድዋ ጦር ዘምተውበት ቃርቻም በአድዋ ጦርነት ላይ ሞተ ነገር ግን ሃውልቱን በአዲስ አበባ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አደባባይ ተሰርቷል፡፡የማርያም ታቦት በወቅቱ አሁን ያለበት ስፍራ አላረፈም ነበር፡፡በዚያው መንደር በአቶ ሲፋ ባላ እልፍኝ ለሶስት ዓመት ቆይቷል በመቀጠልም ማህበረሰቡ በማስተባበር አሁን ያለበት ላይ ቤተክርስትያኑ ተገንብቶ እስከ ዛሬ ለ127 አመታት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል
በአሁን ወቅት የተደራጀ መንፈሳዊ አገልግሎት በስድስት ካህናት አባቶች በሁለት መሪጌታዎች 18 ዲያቆናት በ2 ጥበቃና በ2 አቃቢት አማካኝነት ስርዓተ ቅዳሴ ማህሌት ፤ሰዓታት፤ኪዳን፤በመስጠት ለማህበረሰቡ መንፈሳዊ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
