ጉመር ,ጉራጌ ዞን
ያልተዘመረለት ጀግና
አበጋዝ ዳርሳሞ የኬሮ
በ1867 ዓ.ም የሚኒሊክ ጦር በራስ ጎበና ዳጬ አዝማችነት የመጀመሪያውን ጦርነት ሶዶ ጉራጌ ላይ አካሒዶ በድል ተመለሰ ነገር ግን ከ2 አመታት በኋላ ማለትም በ1869 አ/ም በሚኒሊክ የተመራው ታላቅ የሸዋ ጦር በአበጋዝ ዳርሳሞ አዝማችነት የተከላከለው የጉራጌ ጦርን ማሸነፍ አልቻለም ነበር፡፡
ሚኒሊክ አጼ ዬሀንስን በማሸነፍ ከፍተኛ የፖለቲካ ስልጣን የመጨበጥ ምኞታቸውን ዕውን ለማድረግ የዓጼ ዮሀንስን ሃይል በትጥቅና በተዋጊ የሰው ሀይል መስተካከል ስለነበረባቸው ይህንኑ ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ ቁልፍ የሆኑ ክልሎችን የመቆጣጠር አማራጭን ተጠቅመዋል፡፡ በመሆኑም ይህን ለማሳካት የሚያስችሉ አስፈላጊ አካባቢዎችን ማለትም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጲያና ከሰባት ቤት ጉራጌ የሚመጡ ሸቀጦች ልውውጥ ይካሄድ የነበረበትን የቀቤና ገበያ መቆጣጠር ካለው ኢኮኖሚያዊና የሰው ሃይል ጠቀሜታ አንጻር እንደ አማራጭ ከያዟቸው መካከል ነበሩ፡፡
ወዲያውም የአህመድ ግራኝ ጦርነት ካስከተለው ጥፋት ለማሸሽ በወቅቱ ከፍተኛ ዋጋ የነበራቸው የቤተ-ክርስቲያን ቅርሶች በደቡብ ጉራጌ በኩል ዝዋይ ሃይቅ ውስጥ ተደበቆ ስለነበረ ይህንን ሃብት የግል የማድረግ አላማን ለማሳካት በዝዋይ ሃይቅ አካባቢ የነበሩትን የጉራጌ ግዛቶችን ማስገበር ወደ መንበረ- ስልጣን የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያፋጥን መስሎ ስለታያቸው እንደነበረ የተለያዩ የታሪክ ፀሀፍት ይጠቅሳሉ፡፡
የጉራጌ ህዝብ የዓጼ ሚኒሊክን የግዛት ማስፋት ዘመቻን በመቃወም ለአስራ አራት አመታት መፋለሙን መዛግብቶች ቢገልጹም የጥንት ታሪክ አዋቂ አዛውንቶች ደግሞ የጉራጌ ህዝብ ከንጉሱ ጋር ትግል ያካሄደው ከ20 ዓመታት በላይ እንደሆነ በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡
የጉራጌ ህዝብ ከረጅም ዘመናት በፊት በነገስታት -ዜና መዋዕል ውስጥ ከገባር ግዛቶች አንዱ እንደነበረ ቢጠቀስም ጉራጌ የራሱ ግዛትና አስተዳደርን ለመሸራረፍ የመጣን ሃይል በፀጋ የተቀበለበት ጊዜ እንዳልነበረምእንዲሁ ፡፡ጉራጌ የሃይል አገዛዝን በመቃወም በጀግንነት ያካሄደውን ትግል እ.ኤ.አ ከ(1628-48) ቄስ ፌራንዴዝ በመጽሐፋቸው ላይ የገለጹትን ዊሊያም ሻክ እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡
‹‹ የንጉስ ሱስንዮስን ትዕዛዝ አሻረኝ ያሉ በፈረስ ላይ ሆነው በቀስት የሚዋጉ ጉራጌ ተብለው የሚጠሩ ህዝቦች ናቸው ›› ….ይህ አባባል የጉራጌ ህዝብ የረዥምና የቅርብ ጊዜ ታሪክ ለነገስታት የመገዛት ፍላጎት እንዳልነበረው የሚያስገነዝብ ሲሆን የዓጼ ሚኒሊክ አስተዳደርም የጉራጌን ህዝብ ሙሉ በሙሉ ከመቆጣጠሩ በፊት ቀደም ባለው ጊዜም ብልህ አለቃን ከመካከሉ መርጦ እራሱን በራሱ ሲያስተዳድር መቆየቱን ያመላክታል ፡፡
የጉራጌ ህዝብ የተጋድሎ ታሪክን መነሻ በማድረግ ከላይ ለመግለጽ በሞከርኩት ቁንጽል ታሪክ ውስጥ ለዘመናት ያልተዘመረላቸው የጦር ሰው ታላቅ ጀግንነታዊ አሻራ ይገኛል፡፡ እኝህ ጀግና በጉራጌ ብሄረሰብ ውስጥ ጉመር ወረዳ አሰለጫ ተብሎ ከሚጠራ መንደር የተገኙ ናቸው፡፡…አበጋዝ ዳርሳሞ የኬሮ ፡፡
ታላቁ የጦር ሰው አበጋዝ ዳርሳሞ ኬሮ በተለያዩ ወቅቶች መክተው የመለሷቸውን የሸዋ ጦር ሰራዊት ታሪካዊ ተጋድሎን ለመዘከር የነበረኝን ፍላጎት መነሻ በማድረግ እርሳቸውን በቅርብ የሚያውቁ ታሪክ አዋቂ ከሆኑ የአገር ሽማግሌዎች ጋር ባደረግሁት ቃለመጠይቅ እዚህም እዚያም የተነሱ ተመሳሳይ መልክ ያላቸው ነገር ግን የዚህን እውነተኛ የተጋድሎ ታሪክ ተዓማኒነት የማያደበዝዙ አፈ-ታሪክ መሳይ ወጎችን የቀራረምኩ ቢሆንም ባንጻሩ ደግሞ በጉራጌ ህዝብ የተጋድሎ ታሪክና በአበጋዝ ዳርሰሞ ኬሮ አንጸባራቂ የጀግንነት ታሪክ ላይ ሚዛን የደፋ ኢ- ተአማኒነት እንዳይከሰት ብርቱ ጥንቃቄ በማድረግና ከጉራጌ ህዝብ የተጋድሎ ታሪክ መዛግባታዊ ሰነድ መሰረታዊ ጥናት ጋር በማይጣረስ መልኩ አንዳንድ ወጎችን እነደወረደ ለማስቀመጥ ሞክሬያለሁ….
በመተም ባነም ሶሬሳ፤ቲዩጂ ዳርሳሞ በሳ
በዳቁነ አጀብ ተረሳም፤ ሚኒሊክ ከናም በግስግሳ
ሽኩሽኩየ ሟርድ ተጓሳ፤ያረቅጥ ደንበር ወቀሳ
…………..ፏር ተፏር ቦጠቄ ኔሳ
አበጋዝ ደርሳሞ ዮንደ ሰሜ ተጊነ ነሳ
በሞተ ጋሞ ጭን ሰብ ይትረሳ፤፤
አጤ ሚኒሊክ ያበጋዝ ዳርሳሞ ፈጠመም ጎሳን
……….ወሰደም ክርስትና ባንኮበር ነሳን!!
አጼ ሚኒሊክ የጉራጌ ህዝብ ክልልን በግዛቱ የመቆጣጠር ምኞቱን እውን ለማድረግ የመጀመሪያውን ጦር በ1867 ዓ.ም በራስ ጎበና ዳጨ አዝማችነት ወደ ጉራጌ ላከ፡፡
እራስ ጎበና በሶዶ ጉራጌ ባደረገው ጦርነት እድል ከርሱ ጋር ሆነችና በድል ተመለሰ፡፡ ሆኖም በ1869 ዓ.ም በንጉስ ሚኒሊክ አዝማችነት ጦርነት የከፈተው ታላቁ የሸዋ ሰራዊት በየ አካባቢው በነ አበጋዝ ዳርሳሞ በተመራው የጉራጌ ጦር ተሸንፎ መመለሱን በጉራጌ ትውፊት ተመዝግቧል፡፡ ከዚህም ባሻገር በተለያዩ ወቅቶች ዋና ዋና የሸዋ ጦር መሪዎች ወደ ጉራጌ ሀገር ዘምተዋል፡፡
ከነዚህም መካከል እራስ ወልዴ አሻግሬ ፤ደጃዝማች ገርማሜ ወልደሐዋርያት፤ ደጃዝማች በሻህ አቦይ፤ ፊት አውራሪ ገራዶ ጎበና ፤ፊት አውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ፤ ራስ ጎበና ዳጩ፤ ደጃዝማች መሸሻ ሰይፉ፤ ራስ ሙሉጌታ እና ሌሎችም እንደነበሩ ከታሪክ መዛግባት አካለ ገጽ ላይ ሰፍሯል፡፡
…. ጣኔ ጣኔ ፈትን
ፈቴ ፈቴ በድን
ምርጥ ያበጋዝ ዳርሳሞ ፈርን….
