ጉመር ,ጉራጌ ዞን
“ጀፎረ”/”ጀፎሮ”
ጀፎረ በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ልዩ ታሪክ እንዳለው ይነገርለታል። ጀፎረ አገልግሎቱ ሁለገብ ነው። ለመንደሮች ውበት መላበስ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል።ጀፎረ ማለት የመንደር ወይም የጎጥ ነዋሪዎች የጋራ መጠቀሚያ፣ መተላለፊያ፣ መግቢያ እና መውጫ፣ ሰፊ መሰብሰቢያ፣ ጠዋት ከብቶች ከመሰማራታቸው በፊት ማታ ደግሞ ወደ ቤታቸው ከመግባታቸው በፊት ለማቆሚያነት የሚያገለግል የጋራ ስፍራ ማለት ነው።ጀፎረ የጎኑ ስፋት ከ30-150 ሜትር፣ ርዝመቱ በመሃል የሚያልፍ ገደል፣ ደን፣ ወንዝ እስከሌለ ድረስ ሳይቋርጥ ይቀጥላል። ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የሚለካው በዘፈቀደ ሳይሆን በባህሉ በተመረጡ አባቶች ወይም “የዥር ዳነ” የመሬት ልኬት ዳኞች አማካኝነት መሆኑን የዘርፉ አጥኚዎች ይናገራሉ።



የጉራጌ ማኅበረሰብ ለጀፎረ ትልቅ ትኩረት ከመስጠቱ የተነሳ ጀፎረ ላይ የተተከለ የዛፍ ቅርንጫፍ፣ አፈር ወይም ሌሎችንም ነገሮች ይዞ ወደ ግል ቤት ማስገባት ክልክል ነው።ጀፎረ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች አሉት። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል፦ ሰው ሲሞት የለቅሶ ሥነ ሥርዓት ይከወንበታል፤ ሰርግ ሲኖር የሙሽሪትና የሙሽራው አጃቢዎችና ዘመዶች በባህላዊ ዘፈን በማጀብ ይሞጋገሱበታል፤ ባህላዊ የእርቅ ሥነ ሥርዓት ይከናወንበታል፤ ሕፃናት ይጫወቱበታል፤ በቅሎና ፈረስ ይገራበታል፤ ወጣቶች የገና ጨዋታ ይጫወቱበታል፤ ወንዶችና ሴቶች የደቦ ሥራ ለመሥራት ቁጭ ብለው ይመካከሩበታል፤ በመስቀል በዓል አዛውንት ወይም የቀዬው ሽማግሌዎች፣ ጎልማሶች እና ወጣቶች በደመራው ሥነ ሥርዓት ላይ ተሰብስበው ይመራረቁበታል፤ አባቶች በርጩማቸውን ይዘው በመውጣት ንፁህ አየር ይቀበሉበታል።
ይህ “የመንደር አደባባይ” ለከብቶች መዋያነትም ያገለግላል። በተለይ በክረምት ወራት ከሰኔ እስከ መስከረም የግርጌ ሳር ከከብቶች መብልነት አልፎ ለቤት ክዳን መክደኛነት እስኪደርስ ድረስ እንደማስተንፈሻ ግልጋሎት መስጠት ሌላኛው የጀፎረ ተጨማሪ ጠቀሜታው ነው።በጉራጌ ብሔረሰብ እያንዳንዱ የመንደሩ ነዋሪ ጀፎሮን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት አለበት። የመንደሩ ማኅበረሰብ በዘመቻ መልክ በመውጣት በባለቤትነት ስሜት ጀፎሮን ያፀዳል።በጉመር ወረዳ ከሚገኙ ውብ ጀፎሮዎች መካከል የጣጠራ ጀፎረ እና ጉልቾ ጀፎረ ይጠቀሳሉ።
የጣጠራ ጀፎረ
በጉመር ወረዳ ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ከሚገኙ ባህላዊ ጀፎሮዎች ውስጥ የጣጠራ ጀፎረ አንዱ ነው፡፡ይህ መንደር(ጀፎረ) ለዘመናዊ የመንገድ ጥርጊያ ሳይነካ ለዘመናት ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ቆይቷል፡፡ ከጥንት ጀምሮ አሁን እስካለበት ድረስ የተለያዩ ግልጋሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል ከነዚህም ዉስጥ ለባህላዊ ዳኝነት የሚሰጠው ግልጋሎት በግንባር ቀደምነት ይነሳል፡፡ከባህላዊ ዳኝነት ባሻገር ሌሎች የተለያዩ ግልጋሎቶችን ይሰጣል ከነዚህም ውስጥ የተለያዩ ክብረ በዓላትን ለማክበር ፣ የለቅሶ ስርዓት ፣ ሰርግ፣ባህላዊ በዓላቶች የመሳሰሉትን ለማካሄድ ያገለግላል፡፡የጣጠራ ጀፎረ በጉመር ወረዳ የሸሬብና የጣጠራ ቀበሌ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን 5 ኪ.ሜ እርዝማኔ እንዲሁም 44 ሜትርየጎን ስፋት አለው፡፡
ጉልቾ ጀፎረ
ጉልቾ ጀፎረ የሚገኘው በጉራጌ ዞን በጉመር ወረዳ አበኬ ቀበሌ ሲሆን እጅግ ውብና ማራጂ ገጽታን ተላብሰው ከሚታዩ መንደሮች (ጀፎሮዎች) አንዱ ነው፡፡ ከጉመር ወረዳ አረቅጥ ከተማ በ 5ኪ.ሜ ችቀት ላይ ይገኛል፡፡ ጉልቾ ጀፎረ ልክ እንደሌሎቹ ሁሉ ዘርፈ ብዙ ግልጋሎቶችን ይሰጣል ከነዚህም ውስጥበ ለባህላዊ ዳኝነት፣ ባህላዊ በዓላት( አንትሮሽት) የለቅሶ ስርዓት ፣ሰርግ ፣ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ፣ ክብረ በዓላት ፣ በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ ተሰቷቸው በስፋትና በድምቀት የሚከበሩት መስቀል እና አረፋ ከብዙ በጥቂቱ በዚህ ውብና ማራኪ የጉልቾ ጀፎረ የሚከወኑ ተግባራቶች ናቸው
