ጉመር ,ጉራጌ ዞን
በራስ አቅም ችግሮች ለመቋቋምና እንዲሁም ወቅታዊና ቅጽበታዊ አደጋዎችን ለመከላከል በጉራጌ ዞን እየተሰራ ያለው ስራ ለሌሎች አካባቢዎች አስተማሪ እንደሆነ ተገለፀ።
በማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽፈት ቤት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ማዕከል 2ተኛ ዙር የብልጽግና ፓርቲ ስልጠና ላይ እየተሳተፉ ያሉ አመራሮች በጉመር ወረዳ በራስ አቅም ለመጠባበቂያ እህል ክምችት የለማ ማሳ ፣ በበጋ ወራት በተቀናጀ ተፋሰስ በጠረጴዛማ እርከን የለማ መሬት የገብስ ማሳና እንዲሁም የቦባና የአረቅጥ ሐይቅን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሀላፊና የጉራጌ ዞን ወልቂጤ ማዕከል የ2ተኛው ዙር የአመራሮች ስልጠና አስተባባሪ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ እንዳሉት ” በመደመር መንግስት የዘርፎች እምርታ” በሚል መሪ ቃል በግብርና ትራንስፎርሜሽን ፣ በኢንደስትሪ፣በከተማ ልማት ዘርፍና በቱሪዝም ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
አመራሩ በንድፈ ሀሳብ የወሰዳቸው ስልጠናዎች በተጨባጭ መሬት ላይ ምን አለ የሚለውን ለማስገንዘብ ጉብኝቱ የስልጠናው አካል ተደርጎ እንደተወሰድ አስረድተው አመራሩ ማነቆዎችና ተግዳሮቶችን በመፍታትና በተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ እድሎችን የሚያይ መሆን እንደሚገባው አመላክተዋል።
በጉመር ወረዳ ላይ በግብርናው ዘርፍ ላይ በተለይም የተቀናጀ የግብርና ስራ በተጨባጭ ውጤት የታየበት እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሙስጠፋ ከዚህ በፊት የተጎዳና በአሲዳማነት የተጠቃ መሬት በማከም በሚያምር ሁኔታ ምርት እያመረቱበት እንደሆነና በዚህም ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበትና ሌሎችም አካባቢዎች ሊሰፋ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በራስ አቅም ድህነትን ለማሸነፍ ፣ተረጂነትን ለመሻገር በጉራጌ ዞን እየተሰራ ያለውን ስራ የሚበረታታና በተጨባጭ ውጤት እየታየበት እንደሆነ ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ሀላፊና በጉመር ወረዳ የሰልጣኞች ጉብኝት ቡድን አስተባባሪ አቶ አብዶ ሀሰን እንዳሉት 2ኛው ዙር የብልጽግና ስልጠና በወልቂጤ ማዕከል ከ9 መቶ በላይ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና እየተሳተፉ ይገኛል።
ስልጠናው የገጠር ግብርናው ትራንስፎርም እናደርጋለን የሚል እንደነበርና የግብርናው ትራንስፎርሜሽን እንዴት ወደ ኢንዱስትሪው እያመራና ከተሜነት ማዘመን አለብን የሚል እንደነበረም አመላክተው ይህንንም በተግባር ደረጃ በወረዳዎቻችን ምን አለ የሚለውን ነገር ለመመልከት ሰልጣኞች በሰባት ወረዳዎች ተዛዙረው የመስክ ምልከታ ማድረጋቸውም ተናግረዋል።
በጉመር ወረዳ በጆምቦሮ ቀበሌ በራስ አቅም እንዴት መቋቋም እንደሚቻልና የትኞችም ችግሮች ቢመጡ እንዴት መቋቋም እንደሚቻል በ10 ሄክታር መሬት ላይ ኩታገጠም የገብስ ማሳ አንዱ ማሳያ እንደሆነና በአምዶም ቀበሌ ላይ የተጎዱ መሬቶች በጠረጴዛማ እርከን 50 ሄኬታር ኩታ ገጠም ማሳ አርሶ አደሮች ማልማት እንደቻሉም በአካል ያዩበት እንደሆነም ጠቁመዋል።
የጉመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ከድር በበኩላቸዉ በወረዳው ብልጽግና ለማረጋገጥና የአርሶአደሩ ህይወት ለመቀየር ሰፋፊ እቅዶችን በማቀድና ማህበረሰቡን በማሳተፍ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አስረድተዋል።
አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን በተጨባጭ ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በትራክተር የማረስና በኮንፓይነር ምርት የመሰብሰብ ስራ በስፋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የአርሶአደሩ የተበጣጠሰ ማሳ ወደ በኩታ ገጠም በማጣመር እየተሰራ ሲሆን በዚህም የአምዶምና የድርቦሰነ ቀበሌዎች የ41 አርሶአደሮች በጋራ ሆነው 50 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እያለሙ እንደሆነም አስረድተዋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነት በየአመቱ እየጨመረ እንደሆነ አመላክተው በወረዳው በኩታ ገጠም እርሻ 3550 ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ እንደሆነም አብራርተው ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት 30 ሄክታር መሬት በማሳ መሸፈኑም ጠቁመዋል።
በአምዶምና በጆምበሮ ቀበሌዎች ተዛዙረዉ የተመለከቱት የግብርና ስራዎች በተጨባጭ ውጤት የታየበትና በተለይም ለረጅም አመታት በኢንቨስትመንት ተይዞ ሳይለማ የቆየ መሬት በመረከብ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚል መሬቱን በማረስ በገብስ ያለሙበት ሁኔታ የሚበረታታ እንደሆነና በአካባቢያቸው እንደሚያሰፉትም አስረድተዋል።
የአርሶአደሩ ተናቦና ተቀናጅቶ የመስራት ባህሉ እያደገ እንደሆነ የተናገሩት አስተዳዳሪው እነዚህ በኩታ ገጠም እያለሙ ያሉ አርሶአደሮች ቴክኖሎጂ በጋራ በመጠቀም፣ ሲታረስ በጋራ ያሳርሳሉ ፣ አረም በጋራ የሚያርሙና ምርት በጋራ የሚሰበስቡ እንደሆነም አስረድተዋል።
በጉብኝቱ ከተሳተፉ ሰልጣኝ አመራሮች መካከል አቶ ሊሊ ሙደሲር እና ወይዘሪት ስንታየሁ ተመስገን በሰጡት አስተያየት ስልጠናው የተነሱ በተለይም ከግብርና ትራንስፎርሜሽን እስከ ቱሪዝም በጉራጌ ዞን ውስጥ አለ ወይ በማለት የተደመሙበትና ባዩት የግብርናና የቱሪዝም ሀብቶች የተደሰቱበት እንደሆነም ተናግረዋል።




